msl_AwdeQelem_wana3_1_2008011602

፹ኛ

መታሰቢያ ።


ርእስ ፤ የድል ፡ በዓልን ፡ 80ኛ ፡ ዓመት ፡ መታሰቢያ ፡ ዐብረን ፡ እናክብር ።

ለንደን ፥ መጋቢት ፡ 29 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ።

ክቡራትና ፡ ክቡራን፤

ዘንድሮ ፥ ሚያዝያ ፡ 27 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ የድል ፡ በዓልን ፡ ለ80ኛ ፡ ጊዜ ፡ ስናከብር ፥ ይህ ፡ ሀገራዊ ፡ ድል ፡ ለሀገራችን ፡ ኢትዮጵያና ፡ ለሕዝቧ ፡ ያመጣላቸውን ፡ በረከት ፡ በታላቅ ፡ ባለዕዳነት ፡ እናስባለን ፤ የቀደሙ ፡ ትውልዶችንም ፡ መሥዋዕትነትና ፡ ሰማዕትነት ፡ ዐብረን ፡ በኅሊና ፡ እናስታውሳለን ።

በረከቱም ፡ እንዳይታጣ ፥ መሥዋዕትነቱና ፡ ሰማዕትነቱም ፡ ዋጋቸው ፡ እንዳይዘነጋ ፥ ትውልዶች ፡ ነቅተው ፡ ሊጠብቋቸው ፣ ሊያስታውሷቸውና ፡ ሊያከብሯቸውም ፡ ይገ፟ባ፟ል ። በተለይ ፡ ደግሞ ፥ በዘመኑ ፡ (1928-1933 ፡ ዓ.ም.) ፡ ውድ ፡ ዋጋ ፡ የከፈሉልንን ፡ እናቶችና ፡ አባቶች ፡ በየግላችን ፡ ለማወቅ ፡ የታደልን ፡ የሥጋም ፡ የመንፈስም ፡ ልጆቻቸው ፥ ገድላቸውን ፡ ብንዘክርላቸው ፡ ደስታችንም ፡ ክብራችንም ፡ ስለሚኾን ፥ ይህኑ ፡ ለማድረግ ፥ የልዩ ፡ ልዩ ፡ ቤተሰቦችን ፡ ምስክርነት ፡ በዘመኑ ፡ የማወራኛ ፡ ዐቅም ፡ አዘጋጅቶና ፡ መዝግቦ ፡ ለመጪው ፡ ትውልድ ፡ ለማውረስ ፡ ይበጀን ፡ ዘንድ ፥ ሥራውን ፡ ባስተባባሪነትና ፡ ባዘጋጅነት ፡ ለማከናወን ፡ ስለ ፡ ተነሣሣኹ ፥ ርስዎም ፡ ሊተባበሩ ፡ ፈቃደኛ ፡ ይኾናሉ ፡ በሚል ፡ እምነት ፥ የዝግጅቱን ፡ ዐጪር ፡ መግለጫ ፡ እንደሚከተለው ፡ ዘርዝሬ ፥ የሚሳተፉበትን ፡ መንገድ ፡ ለመምረጥ ፡ ይበጅዎ ፡ ዘንድ ፥ የሱታፌውን ፡ ዝርዝር ፡ መምረጫ ፡ አስከትዬ ፡ አምልክቼያለኹ ።

ክፍል ፡ 1 ፤ የዝግጅቱ ፡ አካኼድ ።

1.1 ፤ ዝግጅቱ ፡ በድምፅ-እና-ርእይ ፡ (audiovisual) ፡ መልክ ፡ ይዘጋጃል ፤ ርዝመቱም ፡ ከ30 ፡ ደቂቃ ፡ እስከ ፡ 45 ፡ ደቂቃ ፡ ይኾናል ።
1.2 ፤ ከእያንዳንዱ ፡ ተሳታፊ ፡ ከ3 ፡ እስከ ፡ 5 ፡ ደቂቃ ፡ የሚፈጅ ፡ የቃል ፡ መልእክት ፡ ይጠበቃል ።
1.3 ፤ ከቃል ፡ መልእክቱ ፡ ጋራ ፡ ዐብሮ ፡ የሚከሠትና ፡ በዓሉን ፡ የሚያደምቅ ፡ የርእይ ፡ (video) ፣ ወይ ፡ የዋካ፟ ፡ (photo) ፡ ወይም ፡ የጽሑፍ ፡ ሰነድ ፡ ሊቀርብ ፡ ይችላል ።
1.4 ፤ የቃል ፡ መልእክቱ ፡ በክፍል ፡ 2 ፡ በሚዘረዘሩት ፡ ርእሶች ፡ መሠረት ፡ ኾኖ ፥ በስድ ፡ ንባብ ፡ (prose) ፡ ወይ ፡ በግጥም ፡ ሊኾን ፡ ይችላል ።
1.5 ፤ ዝግጅቱ ፡ ለሚያዝያ ፡ 27 ፡ እንዲደርስ ፥ የቃል ፡ መልእክቶች ፡ ዅሉ ፡ እስከ ፡ ሚያዝያ ፡ 12 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ ላዘጋጁ ፡ መድረስ ፡ ይኖርባቸዋል ።
1.6 ፤ የቃል ፡ መልእክቶቹ ፡ ባዘጋጁ ፡ በስልክ ፡ ሊቀ፟ዱ፟ ፡ ይችላሉ ፤ በሌላም ፡ መንገድ ፡ እንዲካኼድ ፡ ቢፈለግ ፥ ካዘጋጁ ፡ ጋራ ፡ መነጋገር ፡ ይቻላል ።
1.7 ፤ ዝግጅቱ ፡ ከተጠናቀቀ ፡ በዃላ ፥ በኢንተርኔት ፡ የሚታይ ፡ ይኾናል ፤ የሚታይባቸውም ፡ መርበቢያዎች ፡ (websites)፦
www.awde-qelem.net
www.gzamargna.net እና
www.slttunhzb.net
ብቻ ፡ ይኾናሉ ።
1.8 ፤ ዝግጅቱ ፡ በነጻ ፡ ለሕዝብ ፡ እይታ ፡ ይቀርባል ፤ ለምንም ፡ ዐይነት ፡ ንዋያዊ ፡ ትርፍ ፡ በፍጹም ፡ አይውልም ፥ ዛሬም ፡ ወደፊትም ።
1.9 ፤ ዝግጅቱ ፥ የበዓሉን ፡ ክብር ፡ በጠበቀና ፡ የተሳታፊዎችን ፡ ክብርና ፡ ጥቅም ፡ በጠነቀቀ ፡ መንፈስ ፡ ይከናወናል ።

ክፍል ፡ 2 ፤ የሱታፌ ፡ ዝርዝር ፡ መምረጫ ።

ተሳታፊዎች ፡ ለጥቆ ፡ በተመለከቱት ፡ ጥያቄዎች ፡ መሠረት ፡ አቅርቦታቸውን ፡ ሊለዩ ፡ ይችላሉ፦

2.1 ፤ በርስዎ ፡ አስተያየት ፡ የሚያዝያ ፡ 27 ፡ ድል ፡ ዋነኛ ፡ ፋይዳ ፡ ምንድን ፡ ነው ፡ ይላሉ ?
2.2 ፤ የዐርበኝነት ፡ ዘመንን ፡ በተመለከተ ፡ (1928-1933 ፡ ዓ.ም.) ፥ ትውልዱ ፡ ሊያውቀው ፡ ይገ፟ባ፟ል ፡ የሚሉት ፡ ከቤተሰቦችዎ ፡ ያገኙትን ፡ ታሪካዊ ፡ መታሰቢያ ፡ ቢያካፍሉን ? ርስዎም ፡ በዘመኑ ፡ የዐይን ፡ ምስክር ፡ ኾነው ፡ ቢኾን ፥ መታሰቢያዎን ፡ ቢነግሩን ?
2.3 ፤ በቀጥታም ፡ ኾነ ፡ በተዘዋዋሪ ፡ የዐርበኝነትን ፡ ዘመን ፡ የሚተርክ ፡ መጽሐፍ ፡ ያዘጋጁ ፡ እንደ ፡ ኾነ ፥ እንዲያስተዋውቁን ፡ ዕድሉን ፡ እንሰጣለን ።
2.4 ፤ በዐርበኝነት ፡ ዘመን ፡ ዋጋ ፡ ከከፈሉልን ፡ ዠግኖች ፡ ሰማዕታት ፡ ዅሉ ፥ ማንን ፡ በተለይ ፡ ያደንቃሉ ? ለምን ?
2.5 ፤ የዐድዋ ፡ ድል ፡ በጥቂት ፡ ቀናት ፡ ሲጠናቀቅ ፥ ይኸኛው ፡ ዐምስት ፡ ዓመታትን ፡ መፍጀቱ ፡ ለምንድን ፡ ነው ፡ ይላሉ ?
2.6 ፤ ከ80 ፡ ዓመታት ፡ በዃላ ፥ ዛሬ ፡ አገራችን ፡ ኢትዮጵያ ፡ የምትገኝበት ፡ ኹኔታ ፡ ዳግም ፡ አሳሳቢ ፡ ኾኗል ፤ ለምን ፡ እና ፡ እንዴት ፡ እዚህ ፡ ችግር ፡ ውስጥ ፡ ገባን ፡ ይላሉ ? መፍትሔውስ ፡ ምን ፡ ይመስልዎታል ?
2.7 ፤ እላይ ፡ ከተመለከቱት ፡ 6 ፡ ጥያቄዎች ፡ የተለየና ፡ ከዐምስት ፡ ዓመቱ ፡ የመከራ ፡ ዘመንና ፡ ከድል ፡ በዓል ፡ ጋራ ፡ የተገናኘ ፡ ጕዳይ ፡ ቢኖር ፥ ርሱን ፡ መሠረት ፡ አድርጎ ፡ መልእክትን ፡ ማስተላለፍ ፡ ይቻላል ።

ለተጨማሪ ፡ ማብራሪያና ፡ ለክንውኑ ፡ ኺደት ፡ አዘጋጁን ፡ ወሌ ፡ ነጋን፦

በስልክ ፤ (ለንደን) 00 44 74 96 54 15 90 (mobile)
00 44 20 82 51 24 92 (landline)

በእ-ጦማር ፡ (email)፤awdeqelem@yegara.net

ማነጋገር ፡ ይቻላል ።

ጕዳዩን ፡ በማክበር ፣ አዘጋጁንም ፡ በማመን ፡ ስለሚፈቅዱት ፡ ትብብርዎ ፡ በቅድሚያ ፡ ልባዊ ፡ ምስጋናዬን ፡ በትሕትና ፡ አቀርባለኹ ።

ካክብሮት ፡ ሰላምታዬ ፡ ጋራ፥

ወሌ ፡ ነጋ ።

ዐውደ፡ቀለም©ወሌ፡ነጋ፥2008፡-፡2013፡ዓ.ም.።
AwdeQelem©Welé Negga, 2015 - 2021 A.D.